Announcements | March 1, 2023

“ፕራይቬት/በግል የሚደረግ ስፖንሰርሺፕ” ምንድን ነው?

የአሜሪካ መንግስት ያዘጋጀው አዲሱ የስደተኞች መቀበያና ማቋቋሚያ መርሃ-ግብር ; በግል የሚደረግ ስፖንሰርሺፕ “ፕራይቬት ስፖንሰርሺፕ” ወይም “Welcome Corps” ተብሎ ይጠራል::

የባይደን አስተዳደር ስደተኞችን ወደ አሜሪካ አምጥቶ ከማስፈር ጥረት ጋር በተያያዘ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የሥነ-ሕዝብ፣ ስደተኞችና ፍልሰት ቢሮ በቅርቡ እንዳሳወቀው አሜሪካውያን ሥደተኞችን አምጥተው የሚያሰፍሩበትን ዕድል አመቻችቷል፡፡

በዚህ መሠረት በያዝነው አመት ጃንዋሪ 19 የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ Welcome Corps የተባለ አዲስ አሰራር የዘረጋ ሲሆን ይህ አሰራር ቀደም ሲል ፕሬዝዳንት ባይደን ስደተኞችን ስለማስፈር የተዘረጉትን ፕሮግራሞች የማጠናከርና የማስፋፋትን አስፈላጊነት በተመለከተ የሰጡትን ትዕዛዝ ማስፈፀሚያ ነው፡፡ በዚህ መሠረት አዲሱ አሰራር አሜሪካውያን ስደተኞችን በማስፈር ቀጥታ ተሳታፊ የሚሆኑበትን ሁኔታ በማመቻቸት ስደተኞችን ወደ አሜሪካ የማምጣትና የማስፈር አቅምን ይጨምራል፡፡

ይህ Welcome Corps የተባለው በግል ስደተኞችን የማስመጣት የሙከራ አሰራር የተለያየ ሚና በሚኖራቸው 6 ድርጅቶች አማካኝነት የሚፈጸም ይሆናል፡፡ እነዚህን ድርጅቶች የሚመራው የማህበረሰብ ስፖንሰርሺፕ ማዕከል (Community Sponsorship Hub) ይኖራል፣ ድርጅቶቹም ቸርች ወርልድ ሰርቪስ (CWS)፣ ሬፊውጂ ዌልካም ኮሌክቲቭ (RWC)፣ ኢንተግሬትድ ሬፊውጂ እና ኢሚግራንት ሰርቪስ (IRIS)፣ ኢንተርናሽናል ሬፊውጂ አሲስታንስ ፕሮጀክት (IRAP)፣ IRC እና Welcome US ናቸው፡፡

በአዲሱ Welcome Corps አሰራር መሠረት ማንኛውም አሜሪካዊ ዜግነት ያለው ወይም አሜሪካን አገር ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ (ግሪን ካርድ) ያለው ሰው ስደተኛ አስመጥቶ በማስፈር ሂደት ውስጥ ተሳታፊ መሆን ይችላል፡፡ በዚህ አሰራር መሠረት በአንድ አካባቢ የሚኖሩ አምስት ሰዎች አንድ ላይ በመሆን “የስፖንሰር ግሩፕ” ወይም ቡድን በማደራጀት በግላቸው ስደተኛ ወደ አሜሪካን አምጥተው በማስፈር ሂደት ተሳታፊ ለመሆን ማመልከት ይችላሉ፡፡ ይህን ለማድረግ በእነርሱ አማካኝነት ወደ አሜሪካን የሚመጣው ስደተኛ በመጀመሪያዎቹ 90 ቀናት ውስጥ የሚያስፈልጉትን ነገሮች በሙሉ እንደሚያሟሉለት ያረጋግጣሉ ማለት ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ለሚመጣው ስደተኛ መኖሪያ ቤት ማዘጋጀትን፣ ስደተኛውን ከኤርፖርት መቀበል፣ እንዲሁም (ልጆች ካሉት) ትምህርት ቤት ማስመዝገብ እና ለስደተኛው የሚሆን ሥራ ማፈላለግን ይጨምራል፡፡

የግል ስፖንሰር ድርጅቶች (private sponsor organizations) ከላይ በተጠቀሰው አይነት በግላቸው ስደተኛ በማስመጣት ሂደት ውስጥ የሚሳተፉትን ቡድኖች የዕለት ተዕለት ሥራ ይቆጣጠራሉ፡፡ እነዚህ Private Sponsor Organizations (PSO) ቀደም ሲል ስደተኞች የማስፈር ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፡፡ ልምዱ ያላቸው ድርጅቶች ከሆኑ ለግል ስፖንሰር ቡድኖች የአስተዳደርና የቴክኒክ ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡

አዲሱ Welcome Corps ፕሮግራም ተግባራዊ የሚሆነው በሁለት ዙሮች ነው:-

  • ዙር 1: (“Matching”) (“ማገናኘት”):- ይህ ዙር: በአሜሪካ ስደተኞች የመቀበል ፕሮግራም (USRAP) ውስጥ ተመዝግበው ወረፋ በመጠበቅ ላይ ካሉ ስደተኞች መሃል ተመርጠው ለግል ስፖንሰር አድራጊ ቡድኖች የሚሰጡበት ዙር (phase) ነው፡፡
  • ዙር 2: “ Identification’) (“መምረጥ/መለየት”)፡- ይሄኛው ዙር ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው በ2023 ግማሽ ሲሆን የግል ስፖንሰር አድራጊ ቡድኖች ወደ አሜሪካን እንዲመጣ የሚፈልጉትን  (በስደተኛነት  ተመዝግበው ወረፋ በመጠበቅ ላይ ካሉት መካከል) እራሳቸው የሚለዩበት አሰራር ነው፡፡ ይህ ስደተኛውን የመለየት ሥራ የአሜሪካ ስደተኞች የመቀበል ፕሮግራም (USRAP) ጋር እንዲቀናጅ ይደረጋል፡፡=

የዚህ ፕሮግራም አላማ አ. ኤ. አ. በ2023 ዓ.ም. 10,000 የሚሆኑ አሜሪካውያንን በማስተባበር በሁለቱም ዙሮች  በአጠቃላይ5.000 ስደተኞችን  ወደ አሜሪካ እንዲመጡ ማደረግ ነው፡፡ ይህ አዲሱ ፕሮግራም ቀደም ሲል ሥራ ላይ ከነበሩ መርሃ-ግብሮች ጋር ተመሳሳይ ቢመስልም ልዩና የራሱ ባሕርያት ያሉት ሲሆን ለወደፊትም ከሌሎቹ መሰል መርሃ-ግብሮች ጋር የሚቀጥል ይሆናል፡፡

አዲሱ የ Welcome Corps ፕሮግራም መደበኛውን ስደተኞች የማስፈር ሥራ የሚተካ አይደለም፡፡ በግል ስፖንሰር ተደርገው የሚመጡ ስደተኞች መንግስት ለአዲስ ስደተኞች የሚሰጠውን አገልግሎቶች ያገኛሉ፡፡ ይህንንም ለማግኘት ስደተኛ የማስፈር ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን መጠየቅ ይችላሉ፡፡

ማሳሰቢያ:- አገልግሎቱም ሆነ ምዝገባው ክፍያ የለውም!

ለተጨማሪ መረጃ ይህን ይጫኑ

——

ኢሲዲሲ (የኢትዮጵ ኮምዩኒቲ ያዲቨሎፕመት ካውንስል) በአሜሪካ ስደተኞች ተቀብሎ የማቋቋም አገልግሎት የመስጠት ፍቃድ ከተሰጣቸው አሥር  የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አንዱ ነው:: ECDC ከተቋቋመ 40 ዓመታት አስቇጥፘል:: እስከ አሁን ድረስ ECDC ከ60,000 በላይ ከመላው ዓለም የመጡ ስደተኞችን  መልሶ ያቋቋመ ሲሆን : ባለፈው ዓመት ከ7,000 በላይ የሚሆኑ የአፍጋኒስታን ስደተኞችን እንዲሁም በሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች ስደተኞች ከኮንጎ፣ ዩክሬን፣ ሶርያ ወዘተ.  ተቀብሎ : አስተናግዷል።

ECDC ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው በአሜሪካ  የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ፍላጎት ለማሟላት ነው። በሂደት አገልግሎቱን በማስፋፋት ከአፍሪካ ቀንድ የመጡ ስደተኞችን ሲያገለግል ቆይቷል:: በኋላም አፍሪካውያንን እና ከአፍሪካ ውጪ የመጡ ስደተኞችን ተቀብሎ የማቋቋም አገልግሎት እና  የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ድጋፍ በመስጠት ላይ የሚገኝ አንጋፋ ድርጅት ነው::

በአሁኑ ጊዜ ECDC ከመላው ዓለም ኢሚግራንት እና ስደተኞችን ያገለግላል::

ECDC በአዲሱ የWelcome Corps ፕሮግራም ላይ ይሳተፋል.

ለቀጣይ መረጃዎች እባክዎ ድረገጻችንን ይከታተሉ።

ለጥያቄዎች; እባክዎን ኢሜይል አድራሻ info@ecdcus.org ይጻፉልን::